የውብ ጨዋታና የውጤታማ ቡድን አባት የሆነው አሠልጣኝ ስዩም አባተ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሸለበ
የቀብር ስነ-ስርዓቱ ነገ(ዓርብ)በሳሪስ አቦ ቤተክርስቲያን ከቀኑ በ9:00ይፈፀማል።
በእርግጥም የተሠማው የሀዘን ዜና መራር ዕውነት ነው፤የውብ ጨዋታ ፣የውጤታማ ቡድን አባት፣በርካታ ታላላቅ ተጫዋቾችን ያፈራው በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተጫዋችነትና በአሠልጣኝነት የማይነቃነቅ ሀውልት ለመትከል የበቃው አሠልጣኝ ሥዩም አባተ ዳግም ላይመለስ ይህችን ዓለም ተሰናብቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በገጠመው ጠንከር ያለ ህመም አልጋ ላይ ወድቆ የነበረው አሠልጣኝ ሥዩም አባተ በሀገር ውስጥ በጥቁር አንበሳና ቦሌ ጉምሩክ በሚገኝ ሆስፒታል እንዲሁም በውጭ በባንኮክ በህክምና ሲረዳ ቢቆይም ህይወቱን ማትረፍ ባለመቻሉና በዚህች ምድር እንዲኖር የተቆረጠለት ቀን በመጠናቀቁ በዛሬው ዕለት ይህቺን ክፉ ዓለም ተሰናብቷል።
በ1950ዎቹ መጨረሻና በ1960ዎቹ መጀመሪያ የእግር ኳሱን ዓለም ተቀላቅሎ በተጫዋችነት ታሪክ የማይረሳው ውለታን የዋለው አሠልጣኝ ሥዩም አባተ የስልጠናውን ዓለም በመቀላቀል ሁሌም ሲታወስበት የሚኖር ደማቅ ታሪክ ያፃፈ ባለውለተኛ አሠልጣኝ ነው።
አሠልጣኝ ስዩም አባተ በኢትዮጽያ ብ/ቡድን በተለይ በታዳጊ ቡድን የሠራቸው በርካታ ስኬታማ ስራዎች ቢኖሩም በተለይ በቡና ገበያ አሠልጣኝነት በገነባው ቡድንና ቡድኑ በሚከተለው ማራኪ አጨዋወት በብዙዎች ልብ ውስጥ የማይነቃነቅ ሀውልት እንዲተክል ከማድረጉም በላይ ኢትዮጵያ ቡና የደጋፊ ሀብታም እንዲሆን ትልቁን ሚና የተጫወተ ታሪክ የማይዘነጋው ባለውለተኛ ነው።
በቡና ገበያ የአሠልጣኝነት ዘመኑም ሚሊዮን በጋሻው፣ሙሉጌታ ወልደየስ፣መንግስቱ ቦጋለ፣ዬናስ ተሾመ፣ተሾመ(ቀዌ)፣አስራት አዱኛ፣አሸናፊ በጋሻው፣ሳሙኤል ደምሴ ኩኩሻ፣አንዳርጋቸው ሠለሞንና በቅርቡ በሞት የተነጠቀውን አስግድ ተስፋዬን ለስኬትና ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ያበረከተ ታላቅ ባለሙያ ነው።
ከወራቶች በፊት ወደ ታይላንድ ባንኮክ ተጉዞ ለሁለት ወራት የሚጠጋ ጊዜ ህክምናውን ሲከታተል የቆየው አሠልጣኝ ሥዩም ከባንኮክ መልስ በመኖሪያ ቤቱ ተኝቶ ህመሙን ሲያስታምም ቢቆይም በጤንነቱ ላይ መሻሻል ከመታየት ይልቅ እየተባባሰ መጥቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሸልቧል።
የአሠልጣኝ ሥዩም ዜና ዕረፍት ከተሠማ በሃላ በርካታ የስፓርት ቤተሰቦችን ብቻ ስይሆን መላውን ህዝብ ክፉኛ ያስደነገጠ ሲሆን የብዙዎችን ልብም በሀዘን እንዲኮማተር አድርጓል።
በጨካኙና ክፉው ሞት በድንገት የተነጠቀው አሠልጣኝ ሥዩም አባተ ማረፉ ከተረጋገጠ በሃላ ማምሻውን አስከሬኑ ለፍትሀተ ፀሎት ሳሪስ ወደሚገኘው ቅዱስ ያሬድ ቤተክርስቲያን ተወስዶ እዚያው የሚያድር ሲሆን የቀብር ስነ-ስርዓቱም በነገው ዕለት(ዓርብ)ሳሪስ በሚገኘው የአቦ ቤተክርስቲያን ቤተሰቦቹ፣ወዳጅ ዘመዶቹ፣ጓደኞቹ፣አብረውት የተጫወቱ፣የስፖርት ቤተሰቦች፣የሚዲያ ሠዎችና ታላላቅ ሠዎች በተገኙበት ስርዓተ ቀብሩ በክብር እንደሚፈፀም ታውቋል።
የውብ ጨዋታና የውጤታማ ቡድን አባት የሆነው አሠልጣኝ ስዩም አባተ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሸለበ የቀብር ስነ-ስርዓቱ ነገ(ዓርብ)በሳሪስ አቦ ቤተክርስቲያን ከቀኑ በ9:00ይፈፀማል።
Hatricksport team