በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት በሜዳው መቐለ ከተማን ያስተናገደው ጅማ አባጅፋር 1-0 በማሸነፍ ከመሪው ደደቢት ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ አጥብቧል።
በጨዋታው ጅማ አባጅፋር ከፋሲሉ ጫዋታ የተጠቀመውን ሙሉ ለሙሉ በ4-4-2 አሰላለፍ የተጠቀመ ሲሆን በጫዋታውም በይሁን እንዳሻውና በአሚን ነስሩ የሚመራው የአባጅፋር የመሐል ክፍል ኳስን በሚገባ በመቆጣጠር የመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች የተዋበ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን የጎል ሙከራዎችም አልፎ አልፎ ሲታዩበት ነበር ። ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር መቐለ ከተማዎች ከኳስ ኃላ በመሆን በመከላከል በመልሶ ማጥቃት በአማኑኤልና ጋቶች አማካኝነት ጎል ለመሆኑ የሚችሉ ኳሶች ቢሞክሩም የጫዋታው ኮከብ የነበረው አሚን ነስሩ የሁለቱን ግንኙነት በማቋረጥ ተሳክቶለት አምሽቷል። ሆኖም ጅማ አባጅፋር የወሰዱትን የኳስ ብልጫ ወደ ግብ የመቀየር አጋጣሚ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።
መቐለ ከተማዎች ከኳስ ኃላ በመሆን በተደጋጋሚ ጊዜ ሰዓት ማባከንናቸው ከደጋፊው ተቋውሞ ሲቀርብባቸው ተስተውሏል።
በተደጋጋሚ በሄኖክ አዱኛና ሄኖክ ኢሳያስ ወደ ጎል የሚሻሙት ኳሶችን ወደ አጥቂዎቹ ሳምሶን እና ኦኪኪ ጋር ሳይደረስ የመቀሌው በረኛና ተከላካዮች ሲያመክኑ ውለዋል በ16ኛው ደቂቃ ኦኪኪ ከቅጣት ምት የሞከረውን ኳስ ድንቅ ሆኖ የዋለው የመቐለ ከተማው ግብ ጠባቂ ፊሊፕ አቮኖ በሚገርም ብቃት አውጥቶታል። እንዲሁም በ24ኛ ደቂቃ ላይ አሁንም ኦኪኪ ከኮርና የተሻማውን በግንባር በመግጨት አሁንም ፊሊፕ ኢቮኖ አውጥቶበታል። በመቐለ በኩል ጋቶች በ18ኛ ደቂቃ ከግብ ክልል ዉጭ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል እንዲሁም ጋቶች በ29ኛ ደቂቃ ያሻማውን ኳስ አማኑኤል ሞክሮት ዳንኤል አጄይ በቀላሉ ይዞበታል።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው ግማሽ ይበልጥ ጫና ፈጥረው የተጫወቱ ባለሜዳዎቹ አባጅፋሮች ሲሆን መቐለዎች ባንፃሩ አፈግፍገው መጫወትን መርጠዋል በ54ኛው ደቂቃ ሄኖክ ኢሳያስና ዮናስ አንድ ለአንድ ተቀባብለው ሄኖክ ያሻማትን ኳስ በቦታው የነበረው ኦኪኪ በጉሩም ሁኔታ በመግጨት አስቆጥሯል።
ከጎሉ መቆጠር በኋላ ጅማዎች የተሻለ መነቃቃት የታየባቸው ቢሆንም ልዩነታቸውን ሊያሰፋ የሚችል የጎል ሙከራ ቢያደርጉም ጎል ማስቆጠር አልቻሉም ።
ጅማ አባጅፋሮች ውጤቱን ለማስጠበቅ ባለመ መልኩ መላኩ ወልዴን በአሮን አሞሃ በመቀየር አምበሉ ኤሊያስ አታሮን ወደ ቦታው መሐል በመመለስ በኦኪኪ ብቻ በማጥቃት አፈግፍገው መጫወትን ከመጫወታቸው በተጨማሪ የመቀሌም እንቅስቃሴም ረጃጅም ኳሶችን በመጣል ለመጫወት ተገደዋል ።
ሆኖም እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ መቐለዎች የጎል ማስቆጠር አጋጣሚ ለመፍጠር ተቸግረው ታይተዋል ጅማዎች በአንፃሩ በመስመር በኩል በፈጣን ሽግግር አደጋ በመፍጠር ረገድ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል ነገር ግን ጠንካራውን የመቀሌ የመከላከል ብቃት በማለፍ ጎል ማስቆጠር አልቻሉም በ74ኛ ደቂቃ ከኮርና የተሻማውን ኳስ ሳምሶን ቆልቻ ገጭቶት በግብ አናት ላይ ወታለች እንዲሁም በ84ኛ ደቂቃ ላይ ቢስማርክ የሞከረውን ኳስ አጃዬ ይዞበታል ።
ጨዋታውም በጅማ አባጅፋር 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ጅማዎች ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ መቀሌዎች በ17ጫወታ 6ላይ ለመቀመጥ ተገደዋል።
የተጫዋች አስተያየት
አሚን ነስሩ – ጅማ አባ ጅፋር
” ዛሬ በጣም ደስ ብሎኛል የዛሬው ውጤት የደጋፊው ነው ደጋፊው ከዚህም በላይ ይገባዋል ሁሌም እንደዛሬው ከጎናችን ሁኑ በጣምደስ ብሎኛል ደጋፊዎች አወዳችዋለው ”
የአሰልጣኞች አስተያየት
ገብረመድህን ሀይሌ -ጅማ አባጅፋር
“የዛሬው ጨዋታ ጥሩ ነበር። ከመጀመርያው 45 ና በሁለተኛው 45 እንደ መቐለ ከተማ አጨዋወት ስልት ለውጥ አድርገን ተጫውተናል እንዳሰብነውም ተሳክቶልና።
በዚህም አሸነፍን መውጣት ችለናል። በውጤቱም ደስተኞች ነን ማሸነፍ ችለናል፤ ደስተኛ ነኝ።”
ዮሐንስ ሳህሌ- መቐለ ከተማ
“በጨዋታው ተጋጣሚያችን ጅማዎች ጥሩ ነበሩ። በአብዛኛው ከመስመር እሚነሱ ኳሶችን ይሞክሩ ነበር። አብዛኞቹ ሙከራዎች ያልተሳኩ ቢሆንም ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም አሸንፈውን ወጥተዋል። በቀጣይ ጨዋታዎች ኸደ አሸናፊነት እንመለሳለን።”