ትግራይ ስታድየም ላይ የተካሄደው የስሑል ሽረ እና የጅማ አባጅፋር ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።እንግዶቹ ጅማዎች በመጀመርያው አጋማሽ መጨረሻ ላይ በኤልያስ አህመድ አማካኝነት ባገኙት ግብ መሪ መሆን ቢችሉም ባለሜዳዎቹ ስሑል ሽረዎች በሁለተኛው አጋማሽ መጀመርያ ላይ ዲድዬ ሌብሪ ባስቆጠረው ግብ ነጥብ ይዘው ወጥተዋል።
ስሑል ሽረ ባሳለፍነው ሳምንት ፋሲል ከነማን ካሸነፈው ስብስብ አንድ ቅያሪ አድርገዋል፤ነገ ለሙከራ ወደ ቱርክ ሚያቀናው ምንተስኖት አሎ ወጥቶ ወንድወሰን አሸናፊ ገብቷል።ጅማዎች በበኩላቸው በወላይታ ድቻ ከተሸነፈው ምርጥ 11 መሐመድ ሙንታሪ፣መሐመድ ያኩቡ፣ብዙአየሁ እንደሻው፣ኤርሚያስ ኃይሉ፣ሱራፋኤል ዐወል ወጥተው ሰዒድ ሀብታሙ፣አብርሀም ታምራት፣አምረላ ደልታታ፣ኤፍሬም ጌታቸው፣ኄኖክ ገምቴሳ ገብተዋል።
- ማሰታውቂያ -
በፌደራል አርቢትር ተከተል ተሾመ እየተመራ የተጀመረው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ 30 ደቂቃዎች የስሑል ሽረዎች ብልጫ የታየበት ነበር።ባለሜዳዎቹ ከሁለቱም መስመር እየተነሱ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።በተለይ ዲድዬ ሌብሪ ከቀኝ መስመር አሻምቶት ሳሊፍ ፎፎና የመታው ኳስ ከግብ ጎን ለትንሽ ሲወጣ፣ከግራ መስመር አብዱልለጢፍ መሐመድ አሻምቶት ሰይድ ሀብታሙ የመለሰው ኳስ ረመዳን የሱፍ በቀጥታ መትቶት የግቡ ቀዋሚ ብረት መልሶበታል።
በመጀመርያዎቹ 30 ደቂቃዎች ላይ ወደ ጨዋታው ፍጥነት ለመግባት ተቸግረው የነበሩት ጅማ አባጅፋሮች በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል።ጅማዎች ወደ መሀል ሜዳ ተጠግቶ ሲከላከል የነበረውን የስሑል ሽረ ተከላካይ ክፍልን በረጃጅም እና ሰንጣቂ ኳሶች ማስከፈት ችለዋል።የዚህ ማሳይ ሚሆነው ሙከራ ከመሀል ሜዳ የተላከውን ኳስ በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን በቀኝ በኩል የነበረው ኤልያስ መሐመድ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ለግቡ ቅርብ የነበረው አምረላ ደልታታ ተንሸራቶ ለመታት ቢሞክርም ኳሱ ላይ ሳይደርስበት ቀርቷል።በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ኤልያስ መሐመድ ከመሀል የላከው ኳስ ኄኖክ ገምቴሳ ከስሑል ሽረ ተከላካዮች ሾልኮ በመውጣት ከበረኛው ጋር ቢገናኝም በአስገራሚ ሁኔታ ኳሱን ወርቃማውን እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
እድሎችን መፍጠራቸውን የቀጠሉት ጅማዎች በ44ኛው ደቂቃ መሪ ያደረገቻቸውን ግብ በኤልያስ መሐመድ አስቆጥረዋል።ጨዋታው ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነነበረው ኤልያስ መሐመድ ከግራ መስመር ከኄኖክ የተቀበለውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ ስሐል ሽረ መርበብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።
ሁለተኛውን አጋማሽ በፈጣን የመስመር ማጥቃት እንቅስቃሴ የጀመሩት ስሑል ሽረዎች በ46ኛው ደቂቃ የግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ስህተት ታክሎበት በዲድዬ ሌብሪ አማካኝነት የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል።ከግራ መስመር ረመዳን የሱፍ ያሻማውን ኳስ ሰዒድ ሀብታሙ ለመያዝ ሲሞክር በፈጠረው ስህተት ቅርብ የነበረው ዲድዬ ሌብሪ በቀላሉ ሊያስቆጥር ችሏል።ከግቡ መቆጠር በኃላ ጅማዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ መከላከል ላይ ትኩረት አድርገው ተጫውተዋል።በተለይ የመሀል ተከላካዮቻቸው መላኩ ወልዴና ከድር ከይረዲን ስሑል ሽረዎች ከመስመር ሚያሻግሩዋቸውን ኳሶች በሚገባ ሲከላከሉ ነበር።የሳምሶን አየለ ተጨዋቾች ከመስመር እየተነሱ በርካታ ሚባሉ ኳሶችን ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ቢያሻግሩም የጠራ የግብ እድልን ሊፈጥሩ አልቻሉም።በዚህም መሰረት ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።
ውጤቱን ተከትሎ ስሑል ሽረዎች ነጥባቸውን ወደ 16 ከፍ አድርገው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ጅማዎች ነጥባቸውን ወደ 11 ከፍ ማድረግ ችለዋል።