ፋሲል ከተማ በኢትዮጵያ ኘሪሚዬር ሊግ የሚያደርጋቸው የሁለተኛው ዙር ሁሉም ጨዋታዎች በዋልታ ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ከየስታዲየሞቹ እንደሚያገኙ የተነገረ ሲሆን የክለቡ ቦርድ ከኤቢ ማስታወቂያና ኤቨንት አዘጋጅ ጋር ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
ኤቢ ማስታወቂያና ኤቨንት አዘጋጅ ድርጅት ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር በመተባበር ክለቡ ከሜዳው ውጭና በሜዳው በአፄ ፋሲለደስ ስታዳዬም የሚያደርጋቸው የሁለተኛው ዙር ሁሉም ጨዋታዎች በቀጥታ ስርጭት ሽፋን ለተመልካች እንደሚደርሱ የተነገረ ሲሆን ሞደርን ወርልድ የተባለ ድርጅት በአማካሪነት አብሮ እንደሚሰራ ተነግሯል፡፡
ፋሲል ከተማ ከሜዳው ውጭም ሆነ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የቴሌቪዥን የምስል መብት ከገቢው 50% የሚያገኝ ሲሆን ተጋጣሚዎቹ 25% የሚያገኙ ይሆናል፡፡
በቀጣይ ጊዜያት የሁሉም ክለቦች ጨዋታ የቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ለመስጠት ኤቢ ማስታወቂያና ኤቨንት አዘጋጅ ድርጅት ከክለቦች ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን የተናገሩት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አንተነህ ማሃሪ ከኢትዮጵያ ቡና ወልዲያ ከተማና መከላከያ ክለቦች በተጨማሪ ስማቸው ካልተጠቀሱ 2 ክለቦች ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰው የስምምነት ውል ፊርማቸውን በቅርቡ በመፈራረም ወደ ስራ እንደሚገቡ ለሀትሪክ ስፖርት ገልፀዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ኤቢ ማስታወቂያና ኤቨንት አዘጋጅ ድርጅት የወልዲያ ከተማና ፋሲል ከተማ የሚዲያ አጋር በመሆን የክለቦቹን ጨዋታዎች ከአማራ መገናኛ ብዙሃን ጋር በመተባበር በክልሉ ኤፌሞችና በመላው አለም በናይል ሳት የሬዲዮ የቀጥታ ስርጭት ከማስተላለፍ ባሻገር በአማራ ቴሌቪዥን “አፄዎቹ”የተሰኘ ኘሮግራም ዘወትር ዕሮብ ምሽት እንደሚያቀርብ ይታወቃል፡፡
ከስፖንሰር ድርጅቶች ጋር የሚያደርጉት ስምምነት ዛሬ የሚያልቅ ከሆነ ፋሲል ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲዬም የሚያደርጉት 16ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታ በዋልታ ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት የሚያገኝ ይሆናል፡፡