የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ
ሊግ ጨዋታው በምድብ ሶስት ከደቡብ
አፍሪካው ማማሎዲ ሰንዳውንስ፣ ከቱኒዚያው
ኤስፕራንሴ እና ከዲሞክራቲክ ኮንጎው ኤኤስ
ቪታል ጋር በመደልደል ወሳኞቹን የደርሶ መልስ
ግጥሚያዎች የሚያደርግ ሲሆን የመጀመሪያ
ጨዋታውንም በሳምንቱ መጨረሻ ለማድረግ
ረቡዕ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያመራል፤ የቅዱስ
ጊዮርጊስ ክለብ ለእዚህ ጨዋታም ዝግጅቱን
በጥሩ መልኩ እየሰራ ሲሆን ከግጥሚያውም
አበረታች የሚባል ውጤትን ይዞ ለመምጣትም
መዘጋጀቱን የቡድኑ አባላቶች እየገለፁ
ይገኛል፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለጨዋታው
በቅጣት ቀደም ሲሉ በነበሩት ጨዋታዎች
ላይ ሁለት ቢጫ ካርድ የተመለከተውን
አጥቂውን ሳላህዲን ሰይድ እና በቀይ ካርድ
የወጣውን ምንተስኖት አዳነን የሚያጣቸው
ቢሆንም የቡድኑ ተጨዋቾች ግን እነሱን
ተክተው የሚጫወቱ ተጨዋቾች እንዳላቸው
እና በክለባቸው ውስጥም በውድድሩ የተካበተ
ልምዱ ያላቸው ተጨዋቾች ስላላቸው ወደ
ደቡብ አፍሪካ የሚያመሩት ያለምንም ስጋት
እንደሆነም አስተያየታቸውን ሊሰጡን ችለዋል::
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከአፍሪካ ቻምፒዮንስ
ሊግ ጨዋታው ባሻገር እየተወዳደረበት ባለው
የፕሪምየር ሊግ ውድድር እሁድ ዕለት
የወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኘውን ጅማ አባቡናን
በሳላህዲን ሰይድ ብቸኛ ግብ 1ለ0 ያሸነፈ
ሲሆን ይህንን ድል በማግኘቱም መሪነቱን
ሊያጠናክርም ችሏል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጠንካራ ፉክክርን
ባስተናገደበት የእሁድ ዕለቱ ጨዋታው
ጅማ አባቡናን ከሜዳው ውጪ ሊረታው
በመቻሉም ድሉ የቡድኑን ተጨዋቾችና
ደጋፊዎቹንም በከፍተኛ ስሜት ላይ ሆነው
ደስታቸውን እንዲገልፁም አድርጓቸዋል፤
ያገኙት ውጤትም በተለይ ከሜዳቸው ውጪ
በመሆኑና በተለይም ደግሞ የመውረድ ስጋቱ
ካለበት ቡድን ጋር መሆኑም የስኬቱ መጠን
ጣፋጭ እና የተደራረበ እንደሆነላቸውም
ለዝግጅት ክፍላችንም በሰጡን ተጨማሪ ሀሳብ
ሊገልፁልን ችለዋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጅማ አባቡናን
በመርታቱ የአሁኑ ሰአት ላይ የነጥብ
ድምሩን ወደ 52 ከፍ በማድረግ ከተከታዩ
ደደቢት በአራት ነጥብ የራቀ ሲሆን ካለው
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እና ከሚቀሩትም
ግጥሚያዎች አንፃር የሊጉን ዋንጫ ለ14ኛ
ጊዜ እና በተከታታይ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ
የሚያነሳበት ዕድሉም እንደተቃረበም የቡድኑ
ጠንካራ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች አበባው
ቡታቆም በተለይ ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ
አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
- ማሰታውቂያ -
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ወደጅማ ከተማ
በመጓዝ ስኬታማ ድሉን ካገኘ በኋላ የቀጣዩን
ግጥሚያው በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ባለበት
ጨዋታ ምክንያት የማያደርግ ሲሆን ስለ ክለቡ
የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እያደረገ
ስላለው ጉዞ፣ ስለ አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ
ጨዋታቸውና በመሰል ጥያቄዎች ዙሪያ
ከአበባው ቡታቆ ጋር ቆይታን አድርገን
የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶናል፡፡
ሀትሪክ፡- ጅማ አባቡናን ወደጅማ በመጓዝ
ልታሸንፉትና መሪነታችሁንም ልታጠናክሩት
ችላችኋል፤ ጨዋታውን እንዴት አገኘኸው?
በድሉስ ምን ተሰማህ?
አበባው፡– ከጅማ አባቡና ጋር ያደረግነው
ጨዋታ በሁለታችንም መካከል ጥሩ ፉክክር
የተደረገበት ነበር፤ እኛም እነሱም ግጥሚያውን
ለማሸነፍ አጥቅተን ተጫውተናል፤ ሁለታችንም
የግብ እድል አግኝተን እነሱ ሳይጠቀሙበት
ሲቀሩ እኛ ደግሞ ካገኘናቸው የግብ ዕድሎች
ውስጥ አንዱን ተጠቅመንበት ጨዋታውን
በአሸናፊነት ለመወጣት ችለናል፡፡ የጨዋታውን
ሂደት በተመለከተ እስከእረፍት በእንቅስቃሴው
ደረጃ ጥሩ ነበር፤ በኋላ ላይ የአየሩ ከባድ
መሆን፣ የእኛ ተጨዋች ተስፋዬ አላባቸው በቀይ
ካርድ ከሜዳ ለመውጣት መቻሉና ሜዳውም ሰፋ
ያለ በመሆኑ የተቸገርንበት አጋጣሚ ተፈጥሮ
ነበርና ያንን ተቋቁመንም ነው ጨዋታውን
ለማሸነፍ የቻልነው፤ ከግጥሚያውም
የምንፈልገውንና ጣፋጭ የሆነውን ሶስት
ነጥብም ይዘን በመውጣታችንም ለእኛም ሆነ
ለደጋፊዎቻችንንም በጣም ነው ደስ ያለን፤
ያገኘነው ድልም በጣም ትልቅ የሚባልም ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
ዋንጫን አሁን ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንስቷል
ማለት ይቻላል?
አበባው፡- የፕሪምየር ሊጉ ሊጠናቀቅ
አሁን የሶስት ሳምንታት ጨዋታዎች ይቀራሉ፤
እኛ ደግሞ ከፊታችን አራት ጨዋታዎች አሉን፤
የሊጉን ዋንጫ ለማንሳትም አራት ነጥብ ብቻ ነው
የምንፈልገው፡፡ ያ ባይሆን እንኳን ዋንጫውን
ልናነሳ የምንችልበት ሌሎች እድሎችም አለን፤
ስለዚህም የሊጉ ዋንጫ ወደየትም ይሄዳል
ብላችሁ አታስቡ፤ ዋንጫውን ከእኛ ውጪ ሂድ
ብትሉትም ፈፅሞ አይሄድምና ባለን ልምድ
ተጠቅመን 14ኛውን ዋንጫ እና በተከታታይ
ደግሞ 4ኛውን ዋንጫ ወደ ካዝናችን ለማስገባት
እየተቃረብን ነው የምንገኘው፤ በድሉም ዘንድሮ
ምርጥ ድጋፍን ከሰጡን ከደጋፊዎቻችን ጋርም
ሆነን አብረን እንጨፍራለን፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
ዋንጫን ለማንሳት ክለባችሁ የተቃረበው
ከእነሙሉ ጥንካሬው ነው ወይንስ የሌሎች
ክለቦችም ድክመት ታክሎበት?
አበባው፡- የፕሪምየር ሊጉ ፉክክር ላይ
ድክመት ሁሉም ቡድኖች ጋር ያለ እና
የሚኖር ቢሆንም የዘንድሮ ውድድር ላይ እኔ
ብዙ ቡድኖችን እንደተመለከትኳቸው በጥሩ
ብቃት ላይ ሆነው ነው ያገኘኋቸው፤ እኛን
የፈተኑም አሉ፤ ጥቂቶች ላይ ብቻ ነው ድክመቱ
የሚታየው፤ የበፊቱ የሊግ ውድድር ላይ 30 ነጥብ
በእዚህን ወቅት ስትይዝ ለደረጃ የምትፎካከርበት
ወቅት ነበር፤ አሁን ግን ቡድኖች ይሄን የነጥብ
ቁጥር ጨምረው በብዛት ክለቦቹ ላለመውረድ
እየተፎካከሩበት መሆኑ ውድድሩን ሊያጓጓውም
ችሏል፤ በፊት አስራዎቹ ነጥብ ላይ የሚገኙ
ቡድኖች ነበሩ ላለመውረድ ይጫወቱ የነበሩትና
ክለቦች ነጥቡን ጨምረው በእዚያ ደረጃ ላይ
በብዛት መፎካከራቸው ከድክመታቸው ይልቅ
ጥንካሬያቸውን ነው የሚያሳየው እና የእኛም
ቡድን ዋንጫውን ለማንሳት እየተቃረበ ያለው
በጥንካሬው ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ
የምድብ ድልድል የመጀመሪያ ጨዋታችሁን
በሳምንቱ መጨረሻ ከደ/አፍሪካው ክለብ
ማማሎዲ ሰንዳውንስ ጋር ታደርጋላችሁ፤
ከግጥሚያው ምን ውጤት ትጠብቃለህ?
አበባው፡- የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ
ጨዋታ ለእኛ ምን ማለት እንደሆነና ምን
ማድረግ እንዳለብንም በሚገባ እናውቀዋለን፤
ለእዚያም ስንል ክለባችን ለፍልሚያው በጥሩ
መልኩ ተዘጋጅቷል፤ የምድብ ድልድሉ ላይ እኛ
የምንፋለመው በጣም ጠንካራ ከሚባሉት ቡድኖች
ጋር ነው፡፡ ጠንካራ ክለቦችን ደግሞ ከእዚህ ቀደም
ተፋልመን ብቃታችንን በሚገባ አሳይተናል፡
፡ በቅርቡ ከኮንጎው ከለብ ጋር ያደረግነው
ጨዋታ በራሱ በጣም ጠንካራ ነበር፡፡ ከእነሱ
የባሰም ጨዋታ ስለማይገጥመንም ቡድናችን
ከደ/አፍሪካው ክለብ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ
ጥሩ ውጤት ይዞ ይመለሳል ብለን እናስባለን፤
እዚያ በሚኖረን ጨዋታ ለውጤታችን ማማር
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያንና
ደጋፊዎቻችንም ስላሉ የተሻለ ነገር ለመስራትም
ያስችለናልና በጨዋታው ጥሩ እንጂ የከፋ
ውጤት ፈፅሞ እንደማይገጥመን እርግጠኛ ነው የሆንኩት፡፡
ሀትሪክ፡- የደ/አፍሪካውን ማማሎዲ
ሰንዳውንስን በምትፋለሙበት ጨዋታ አጥቂው
ሳላህዲን ሰይድ እና አማካዩን ምንተስኖትን
በቅጣት ታጣላችሁ፤ አይጎዷችሁም?
አበባው፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ
ሁለቱን ተጨዋቾች በተለይ ደግሞ አጥቂውን
ሳላህዲንን በጨዋታው ላይ በቅጣት
የሚያጣው መሆኑ ቢጎዳውም ክለባችን
በውድድሩ ላይ ልምድ ያላቸውን ልጆች መያዝ
መቻሉ እና ውድድሩም ምንእንደሚፈልግም
ስለምናውቅ በሚቻለን መጠን ስፍራዎቹን
በሌላ ተጨዋቾች ሸፍነን በመጫወት
ከመጀመሪያው ጨዋታ ጥሩ የሚባል ውጤት
ይዘን ለመምጣት ተዘጋጅተናል፡፡