THE BIG INTERVIEW WITH ZEMARIAM W/GIYORGIS
ወልዲያን ይዞ በተላለፈበት ቅጣት አይስማማም….አሁን ድረስ ቅሬታ ፈጥሮበታል….
በቅጣቱ ምክንያት ደግሞ ፌዴሬሽኑ የሚያውቀው ውልን ከየትኛውም ክለብ ጋር መፈራረም አልቻለም……ከጅማ አባጅፋር ጋር ኮንትራት ቢኖረውም ህጋዊ ባለመሆኑ
መብቱን መጠየቅ አልቻለም….ረዘም ላለ ጊዜ ያለደመወዝ ሲሰራ የቆየውም ለዚህ
ይመስላል……በተደጋጋሚ ጊዜ ችግሩን ቢናገርም በውስጥ ውል የተፈራረመውን ደመወዝ
ሳይሰጠው ሲቆይ ታግሶ ኖሯል…. ባለፈው ሃሙስ ጠዋት ግን በቃኝ ደመወዜ
እግዚአብሄር ይስጥልኝ መሆኑ ይብቃ ያለ ይመስላል…..ጅማዎችን ተሰናብቶ ከባለቤቱና
ልጁ ጋ ቤቱ ማሳለፍን መርጧል…..አሰልጣኝ ዘማሪያም ወ/ጊዮርጊስ…… ከዮሴፍ
ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ስለውሳኔውና ተያያዥ ጉዳዮች ሰፋ ያለ ምላሹን ሰጥቷል..
ሀትሪክ፡- ከጅማ አባጅፋር ጋር የተለያየኸው የምር በደመወዝ አለመከፈል ብቻ
ነው?
ዘማርያም፡-አዎ… ሌላ ምንም ምክንያት የለኝም፡፡ ከዚህ በፊትም ለ6 ወር ያህል
ከሰራሁ በኋላ ደመወዝ ስላልተከፈለኝ ለማቋረጥ ተገድጄ ነበር፡፡ አሁንም ደመወዝና
ሌሎች ክፍያዎች በአግባቡ ስላልተከፈለኝና ቤተሰብ ለሚያስተዳድር ሰው ከባድ በመሆኑ
ከኃላፊነቴ ለማግለል ወስኛለው፡፡ የእውነቴን ነው የምናገረው ነገሩ ከአቅሜ በላይ
ሆኖብኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ውል ስትፈርም የነበረው ስሜት ምን ይመስል ነበር?
ዘማርያም፡-ስንጀምር ጥሩ ይመስል ነበር፡፡ ቦታው ለመስራት የተመቸ
ነው…..የሜዳው ድባብ የደጋፊው ፍቅር ደስ ይላል፡፡ ችግሩ የአሰራር ክፍተት መኖሩ ነው
ችግር ሲፈጠር የክለቡ አመራሮች ቶሎ መፍትሔ ለመስጠት ይቸገራሉ፡፡ ይሄንን ስራ
ደርበህ ልጆችን ማባለል ከበድ ይላል በተለይ እያቋረጡ ሲጀምሩ ሲታይ ቆይታውን ከባድ
ያደርገዋል፡፡ ከዚህ አንፃር 6ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ አስገራሚና ትልቅ ነገር ነው ብዬ
ነው የማስበው፡፡
ሀትሪክ፡- ደመወዝ ላለመክፈል ትልቁ ምክንያታቸው ምንድነው?
ዘማርያም፡-እንቢ አንሰጥህም ብለውኝ አይደለም ክለቡን ለቅቄ የወጣውት፡፡
አካውንታችን ላይ ገንዘቡ እንደገባ እንሰጥሃለን እያሉኝ ነበር የሚያቆዩኝ፡፡ መጨረሻ ላይ
ልምምድ ሳቆም እባክህ ብለው ሲጠሩኝ የ6 ወር ደመወዘ ካልገባ አይሆንም በተለይ
ከፊርማ ጋር የተያያዙ ጥቅማ ጥቅሜ ካልተከበረ አልፈልግም ስል ይከፈለው የተባለበትን
ቃለ ጉባኤ አሳይተውኝ ተመልሼ ቀጠልኩ፡፡ ከዚያ በኋላ 3 ወር ብጠብቅም ምንም
ተግባራዊ ሊደረግ ባለመቻሉ ራሴን ለማግለል ወስኛለው፡፡
ሀትሪክ፡-ለመጨረሻ ጊዜ ደመወዝ የተከፈለህ መቼ ነው?
- ማሰታውቂያ -
ዘማርያም፡-ታህሰስ ላይ ከፍለውኛል፡፡ 2 ወር ግን ያለ ደመወዝ ሰርቻለው… ቀሪውን
ሊከፍሉኝ ግን አልቻሉም፡፡
ሀትሪክ፡-ድንገት በቃኝ ስትል ከኃላፊነት የመሸሽ የጥፋተኝነት ስሜት አልተሰማህም?
ዘማርያም፡-በፍፁም አልተሰማኝም አይሰ ማኝምም ብዙ ጊዜ ታገስኩኮ፡፡
የሚገርመው የመጨረሻ ጨዋታ ለማድረግ ወደ መቐለ ስንሄድ ከጅማ የመጣሁት እቃዬን
በሙሉ ጠቅልዬ ነው ተመልሼ የምመጣው ደመወዜን ስትከፍሉኝ ቡድኑ ጥገና
ስለሚያስፈልገው ለዝውውር ስትፈቅዱ ነው ብዬ ነገርኳቸው በጎን ግን 4 ተጨዋቾችን
አዘጋጅቼ ነበር፡፡ 5 ቀን እረፍት ሰጥተን ስንመጣ ሁሉ ሁኔታው ሊስተካከል አልቻለም……
ምን እያልኩ ነው ይህን ሁሉ ባላደርግ ነበር የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማኝ፡፡ ትክክለኛ
ማድረግ የሚገባኝን በማድረጌ የጥፋተኝነት ስሜት አይሰማኝም፡፡
ሀትሪክ፡-ለተጨዋቾቹ በወቅቱ ደመወዝ አለመከፈሉ በውጤት ደረጃ ተፅዕኖ
አልፈጠረብም?
ዘማርያም፡- በጣም ይፈጥራል እንጂ.. ጅማ ስሄድ ውሌ ለ2 አመት ነበር…
ሁኔታውን ሳይ ደስ የሚል ነገር አጣሁና አንድ አመት ብቻ መፈረም አለብኝ ብዬ ወደ
አንድ አመት ፈረምኩ….በዚህ ጊዜ ውስጥ ልምምድ ስንሰራ እየተቆራረጠ ነበር የተወሰነ
ጊዜ ሰርተን ይቋረጣል… ምክንያቱም ተጨዋቾቹን ያለ ክፍያ ማስገደድ አልቻልኩማ…
እንደ ክለብ አመራር በተጨዋቾቹ ስነ ልቦና ላይ መስራት ሁሉ ነበረብኝ ቦታው ጫና
የነበረበት ለዚህ ነው፤… አሁን ያለንበት ደረጃ 6ኛ መሆኑ መልካም ነው በዚህ ይለቅልን
እንጂ… በቀጣይ ግን ስሜቱ ተስተካክሎ ውጤቱ ይቀጥላል ወይ ብትለኝ ግን ከፍተኛ ስጋት
አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡-አንድ ታሪክ ሰማሁ…ደመወዝ እየዘገየ ይከፈላል… አንድ ተጨዋች ልምምድ
ዘገየና ምነው ዘገየህ ቢሉት ደመወዜም ይዘገይ የለ ብሎ መለሰ አሉ.. ይሄ ምን ያህል
የዲሲፕሊን መጣስ እንዳለ አያሳይም?
ዘማርያም፡-በጣም… ማስተዳደር የከበደኝ ይሄ ጉዳይ ነው…. ከፈተፈጥሮ ባህርዬ
ወጥቼ ሁሉ እንድሰራ አስገድዶኛል ተጨዋቹ ስህተት ቢሰራምኮ ይሄን ነገር ታሳቢ
ታደርጋለህ ይሄ ግን አግባብ አይደለም፡፡ የክለቡን ስርዓት ሲጥስ ስላልተከፈለው ነው
እያልን መሄዳችን ሁኔታውን ከባድ አድርጎብናል፡፡ ይሄ ቡድኑ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡
ሀትሪክ፡- ተጨዋቾቹ ልምምድ ቀርተ ውብህ ያውቃሉ?
ዘማርያም፡- ብዙ ጊዜ ገጥሞኛል፡፡ አንዴ ሜዳ ላይ ወጥቼ ኮን እየደረደረኩና
እያስተካከልኩ ተጨዋቾቹን እጠብቃለሁ… ለካ እነርሱ ልምምድ ላለመምጣት ተነጋግረው
ቀርተዋል እኔ ደግሞ ይህን አላውቅም፡፡ መኖሪያ ቤታቸው ካምፑ ፎቅ ላይ ሆነው ያዩኛል፡፡
መስኡድ መሀመድ ሲያየኝ አሰልጣኙ ሜዳ ላይ ሆኖ መቅረት አልችልም በማለቱና
በመምጣቱ ሌሎቹ ተሰምቷቸው አንድ በአንድ መጡ… ጉዳዩን ስሰማ በጣም አዘንኩ…
ተደጋጋሚ ተግዳሮት የሆነብኝ ይሄ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-በጅማ አባጅፋር ኃላፊነት ስንት ጊዜ ቆየህ?
ዘማርያም፡-ሀምሌ አጋማሽ ጀምሮ በኃላፊነት አለው… ጅማን እንድወድ ያደረገኝ
በአፍሪካ ደረጃ የተለየ ልምድ እንዳገኝ አድርጎኛል፡፡ የተለየ መልክ ያላቸው ሁለት አይነት
ውድድሮች ያየሁት በጅማ ኃላፊነቴ ነው፡፡ ፕሪሚየር ሊጉና ሻምፒየንስ ሊጉን አጣጥሞ
የመጓዝ ትግል የገጠምኩበትና የተለየ ልምድ ያገኘሁበት ክለብ ነው… አብዛኞቹ
ውድድሮች ከሽቦ ውጩ ከደጋፊ ጋር ሆኜ ነበር ስመራ የነበረውና የህዝቡን ስሜት
በቅርበት ማየቴ መቼ ነው የቴክኒካል ስፍራ ቆሜ ይህን ቡድን የምመራውና ደጋፊውን
የማስጨፍረው የሚል ስሜት ይፈታተነኝ ነበር፡፡ አንደኛ ዙር እስኪልቅ የነበረኝ ስሜት
የተለየ ነበር፡፡ ነገር ግን ከፋይናንስ ጋር ያለው ክፍተት ቅር ያሰኛል፡፡ የቆየሁበት 7 ወር
የሁለት አመት ያህል እንዲርቅብኝ አድርጓል፡፡ ከመስከረም የአዳማው የዝግጅት ጊዜ
ጀምሮ የነበረው የተንጠባጠበ ልምምድ ተቸግሬበታለው፡፡ ሌሎቹ ክለቦች የሀምሌና የነሀሴ
ደመወዝ እየሰጡ ሲያስጀምሩ እዚህ ግን ይህ ነገር የለም፡፡ ሁላችንም ደመወዝ
የወሰድነው ታህሳስ ላይ ነበር እነዚህ ተግዳሮቶችን እያስታመምኩ መኖር ይከብዳል፡፡
መልካሙ ጊዜ ቢበዛም የፋይናንሱ ነገር ፈተና ሆኖብኝ ነበር እንደአሰልጣኝ አልአህሊን
ገጥመህ 2ለ0 ተሸንፈህ ሀገር ቤት ደግሞ 1ለ0 አሸንፎ መውጣታችን ይሄ ትልቅ ስኬት
ነበር…. በተለይ የግብፅና ሞሮኮ እግር ኳስን ከኛ ሀገር ጋር ያለውን ልዩነት ያየሁበት
በመሆኑ ቆይታዬን የማይዘነጋ አድርጎታል፡፡ መልከም ነገሮቹ ይበዛል ትኩረት ማድረግ
የምፈልገውም ይሄንን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ለቡድኑ አባላት ምን ትላለህ?
ዘማርያም፡-አብዛኞቹን ልጆች ያስፈረምኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ግዳጅ መጥቶ መንገድ ላይ
መቆም አግባብ አይ ደለም አብሬያቸው አመቱን ብጨርስ ደስ ይለኝ ነበር ነገር ግን ይሄ
አልተሳካም ለተጨዋቾቼ በቀሪው ጊዜ መልካም የውድድር ዘመን ይሁንላቸው አቅም
አላቸው ረጅም መንገድ መሄድ የሚችሉ መሆናቸውን አውቃለውና በርቱ ማለት
እፈልጋለው፡፡ ለደጋፊዎቻችን ደግሞ አመራር መቼም ሊቀያየር ይችላል እናንተ
የምትደሰቱበት ዘመን እንደሚደገም ተስፋ አደርጋው ጅማ መጥቼ ከናንተ ጋር የምሰራበት
ጊዜ እንደሚኖር እምነቱ አለኝ……ነገ ወይም ሌላ ጊዜ አብሬያችሁ እንደምሰራ ተስፋ
አደርጋለው…….በቀጣይ የደስታችሁ ምክንያት እንደምሆን ተስፋ አደርጋው…. ለአሁኑ ግን
የምትደሰቱበት ጊዜ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-ከፋይናንስ አንፃር ያለው ችግር ቢፈታ ለመመለስ ዝግጁ ነህ?
ዘማርያም፡- መናገር የምፈልገው ከጅማ አባጅፋር የወጣሁት ደመወዜን
ባለመክፈላቸው እንጂ ሌላ ክለብ ፍለጋ አይደለም…. ቤተሰብ እየመራሁ በተጨማሪ
የምረዳቸው ሰዎች እያሉ በዚህ መልኩ መቀጠል ባለመቻሌ ብቻ ነው የወጣሁት፡፡ አቅም
ስላነሰኝ እንጂ ከሌላ ክለብ ጋር አላወራሁም፡፡ አሁንም ቤቴ ነው የተቀመጥኩት….
ከሁሉም ጋር ያለኝ ግንኝነትኮ መልካም ነው፡፡ በትክክል የምፈልገውን ነገር ካደረጉ
ውሳኔዬን የማየው ይሆናል…ከዚህ በፊት ተጓዥ ደጋፊ የማውቀው በተወሰነ መልኩም
ቢሆን በፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ነበር….. ይሄ ስሜት አሁን ደግሞ የጅማ ደጋፊዎች ላይ
አያለውና ይሄን ደጋፊ መተው አዕምሮዬ አይችልም፡፡
ሀትሪክ፡- 2 ወር ያለስራ ያለ ደመወዝ መቀመጥ አይከብድም? የተቆጠበው
እየተበላ ወይስ የጀርባ የፋይናንስ ኃይል አለህ?
ዘማርያም፡-(ሳቅ በሳቅ) ኧረ በፍፁም… ቤተሰብ ስመራ ባለኝ ነው እንቀሳቀስ
የነበረው…. ወደ ኋላ 2 ወር ወደፊትም ቀሪ 3 ወር ያለደመወዝ መኖር ይከብዳል
በርግጥ ወደፊት ምን እንደሚመጣ ባላውቅም ፈጣሪ አንድ ነገር ያመጣል ብዬ
እገምታለው፡፡ ባለሙያ ስለሆንኩ ነገን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ያቋረጥኩትም ስለከበደኝ ነው
ባለፈው አመት ቅጣት ላይ እንደመሆኔ ግማሹን አመት ያለደመወዝ ነበር የኖርኩትና ያ
ሁሉ ሲደመር ትንሽ ከበድ ብሎኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ባለፈው አመት የተላለፈውን ቅጣቱን ተቀብለኧዋል?
ዘማርያም፡-እርሱ በጣም አስቸጋሪ ነው ወደፊት በቅጣቱ ዙሪያ ባወራ እመርጣለው
አስቸጋሪ ጊዜ ነበር በወቅቱ የነበሩ የወልዲያ ብቻ ሳይሆን የፋሲል ከነማ አመራሮችም
ያዩት ጉዳይ ስለነበር ወደፊት በታሪክነት የማነሳው ይሆናል፡፡ በባህሪዬ ዝም ብዬ ማለፍ
ስለምወድ ነው እንጂ ቅጣቱ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ፡፡ የተጎዳ አካል የተቀጣበት ውሳኔ
ነው ወደፊት በተለይ በሌላ ፕሮግራም የማወራው ይሆናል፡
፡
ሀትሪክ፡-የሕግ ሰዎች ስለቅጣት አላማ ሲናገሩ ማስተማሪያ ነው ይሉታል… አንተ
አልተማርኩበትም እያልከኝ ነው?
ዘማርያም፡- እውነት ለመናገር ቅጣት አስተማሪ ነው ቢባልም ከምኑ እንደምማር
አልገባኝም፡፡ምናልባት በዳኞቹና ተጨዋቾቹ መሀል የነበረውን ለማብረድ ሜዳ ውስጥ
መግባቴ ካልሆነ በስተቀር ቅጣቱ ለኔ አሳማኝ አልነበረም፡፡
ሀትሪክ፡-ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ በይበልጥ የሚታወቀው በተጨዋችነቱ? ወይስ
በአሰልጣኝነቱ?
ዘማርያም፡- ስጫወት ያዩኝን ሰዎች አግኝህ ብታናግራቸው ደስ ይለኝ ነበር ምናልባት
የምጫወተውን ያህል ማስልጠን እችላለው ብዬ አላምንም.. ስጫወት ጥሩ አቋ ሜን
አሳይቻለው…. በአጥቂ ወይም በአማካይ ቦታ ስጫወት ጥሩ ነበርኩ፡፡ በተጨዋችነቴ
የጀመርኩት ኒያላ ሺኆን ዛምቢያ ለሄደው ወጣት ቡድን በአሰልጣኝ ስዩም አባተ
ተመርጬ ነበር፡፡ በክለብ ደረጃ አግሬሲቭ ሆኜ ስጫወጽ በቀይ ካርድ በመባረሬ እንዴት
ቀይ ካርድ አየህ ብሎ አሰልጣኝ ስዩም አሰናብቶኛል ሙገር፣ ወንጂ ስኳር፣ ንግድ ባንክ
(ወጣት ቡድን) ተጫውቼ አሳልፌያለው፡፡
ሀትሪክ፡-የአሰልጣኝነት ህይወትህ የት ይጀምራል?
ዘማርያም፡-ወረዳ 4 የሚባል የአካባቢ ቡድን ነበር እንደ አጋጣሚ ነው አሰልጣኝ
የሆንኩት፡፡ ልጆቹን በማስተባበርና በማሰልጠን የወረዳ ዋንጫ ስናሸንፍ የወረዳው
አሰልጣኝ አደረጉኝ፡፡ ወረዳውን ይዤ ዋንጫ ስወስድ.. የዞን አሰልጣኝ አደረጉኝ፡፡ አዲስ
አበባ ላይ አስሩ ክፍለ ከተሞች ሲጫወቱ ዋንጫውን እንደገና አሸነፍኩ፡፡ ያኔ ታድያ ፋሲል
ከነማ አሰልጣኝ ይፈልግ ነበርና ወደዚያው ተጓዝኩ…
ሀትሪክ፡-ከወረዳ ነው በቀጥታ ፋሲል ከነማን የያዝከው?
ዘማርያም፡-አዎ በቀጥታ ነው የሄድኩት፤ ባህርዳር ዩኒቨሲቲ፣ ባህርዳር ከተማ፣
ቡራዩ ከተማ አዳማ ከተማ፣ ባህርዳር ከተማ፣ ፋሲል፣ ወልዲያና ጅማ እያለ የአልጣኝነት
ህይወቴ አሁን ያለበት ደርሷል በነገራችን ላይ ታችኛው ሊግ ላይ የዞን ውድድር ነበር
በአምስት ዞን ተመድቦ የየምድቡ አንደኞች ሌላ ከተማ ላይ ተፋልመው ሁለት ቡድን ወደ
ፕሪሚየር ሊግ ያልፋል፡፡ በሰሜን ዞን የምድብ ውድድር ብዙ ጊዜ አንደኛ ነኝ ዘማርያም
ካለ የምድብ ውድድር 1ኛ ነው ይላሉ..1ኛ ሆኜ ሄጄ ጥሎማለፍ ላይ ስወድቅ
እሰናበታለሁ፡፡ በተለይ ታችኛው ሊግ ስትሰራ ጫፍ ደርሰህ ስትወድቅ አንተም ትባረራለህ
ቡድኑ ይበተናል ሌላ ቡድን ትሄዳለህ ድርጊቱ ይደጋገማል፡፡ 5 ጊዜ ይሄ ውድድር ተካሂዶ
5ቱም ጊዜ አንደኛ ነበርኩ 2007 ፋሲልን ይዤ ድሬዳዋ ሄድኩ የመጀመሪያ 3 ጨዋታ
ስናሸንፍ ፋሲል ፕሪሚየር ሊግ ገባ ሲባል ከ2 ጨዋታ 1 ነጥብ ማግኘት አቅቶን ወደቅን፣
2008 ላይ ፎርማቱ ተቀየረ በሁለት ምድብ ድልድል ይወጣና አንደኛ አንደኛ ወደ
ፕሪሚየር ሊጉ ያልፋል ተብሎ ተወሰነ… ይሄ ለኔ የተሻለ ነበር ለካ የያዘኝ ፎርማቱ ነበር
ፋሲል 4 ጨዋታ እየቀረው 2008 የምድቡ 1ኛ ሆነን ፕሪሚየር ሊግ ገባን፡፡ በተለይ
ባህርዳር ከተማን ይዤ አመቱን ሙሉ ሳንሸነፍ ቆይተን በጥሎ ማለፍ በወልቂጤ በፍፁም
ቅጣት ምት ተሸንፈን ወደቅን ይሄኔ ቡድኑ ተበተነ.. ቀጣይ ሲዝኑን ቢደግም
በርግጠኘነት ያልፍ ነበር፡፡ ያ ቡድን ነው ፋሲል ከነማን ተቀላቅሎ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ
ያለፈው… እዚያ የነበሩት እነ ከድር፣ ሄኖክ… ተከትለውኝ ጅማ አባጅፋር ድረስ አብረውኝ
መጥተዋል፡፡
ሀትሪክ፡-ያንተ ስኬት ተደርጎ የሚታሰበው መቼ ነበር?
ዘማርያም፡-የኔ ብዙ ነገሬ ያለው ፋሲል ከነማ ውስጥ ነው…. ከደጋፊዎቹ ጋር
ቤተሰብ ሆኛለው… ባለቤቴን አግኝቼ ትዳር የመሰረትኩት በፋሲል ቆይታዬ ነው፡፡ ደጋፊ
አይደለችም፡፡ ነገር ግን በየጊዜው የተለያዩ ሆቴሎች ግብዣ እየተካሄደ ሽልማት ይሰጠን
ነበር… በዚያ የሽልማት ቀን ላይ መጥታ ተዋወቅን… ትዳር መስርተን ልጅ ወልደናል፡፡
ባለቤቴ ፅዮን ደረሰ ትባላላች የልጄ ስም ሜሎን ዘማርያም ይባላል፡፡
ሀትሪክ፡-ከቤተሰባችሁ ስፖርት በተለይ እግር ኳስ የነካው ሰው አለ?
ዘማርያም፡-ሰባት ወንድምና አንድ እህት አለኝ፡፡ ጠቅላላ ማለት ይቻላል ስፖርት
ውስጥ ያለፉ ናቸው አብዛኞቹ ኳስ ተጫውተው አልፈዋል ምናልባት እህቴ ብቻ ናት ኳሱን
ያልነካችው.. እናቴ ደግሞ የታወቀች ደጋፊ ናት፡፡ ወረዳ 4 ቡድን ሜዳችን አጠገብ
የቤተሰቤ ቤት ይገኛል፡፡ የኛ ቡድን ካሸነፈ ሙሉ ቡድኑን አንባሻ ጋግራ ታበላለች ቡድናችን
ደግሞ ላለመሸነፍ ዋጋ ይከፍል ነበር ይሄን ይመስል ነበር፡፡
ሀትሪክ፡-በአሰልጣኞች መሀል ውስጥ ለውጥ የመሸርሸር ስራ ይሰራል.. የገጠመህ
ነገር እንዳለ ሰማሁ?
ዘማርያም፡-ጅማ አባጅፋር ይዤ እያሰለጠንኩ አንድ አሰልጣኝ ለከንቲባውና ስራ
አስኪያጁ ሲቪውን ሰጥቶ ነበር፡፡ እኔ ተቀጥሬ በውስጥ ውል ጨርሼ እየሰራሁ መሆኑ
እየታወቀ አሰልጣኙ ቅጠሩኝ ብሎ ጠይቋል፡፡ ይሄ ያሳፍራል.. ከንቲባው ጋር ለስራ ጉዳይ
ገብቼ እየተነጋገርን ሳለ ኧረ አንድ ሲቪ መጥቶልኛል ብሎ መፅሀፍ የሚያክል ሲቪ
አሳየኝ፡፡ በጣም አዘንኩ ሲቪው ዛሬ ተሰጥቶኝ በእጄ ላይ ይገኛል (ሳቅ) ምናልባት አንድ
ቀን ሲመቸኝ ለባለቤቱ ሲቪውን ለመመለስ አዘጋጅቼው እጠብቃለው፡፡
ሀትሪክ፡-ይሄ መወገድ እንዲችል ምን ይደረግ ትላለህ?
ዘማርያም፡-በዚህ ችግር ዙሪያ እንዳንወያይ የአሰልጣኞች ማህበር ጠንካራ አይደለም፡፡
ምናልባት ተነጋግረን መማማር እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በየትኛውም መስፈርት
አሰልጣኝ ባለበት ቦታ ላይ ሌላ ሰው መጥቶ እኔን አስገቡኝ ማለቱ እንደ ስብዕናም ተገቢ
ነው ብዬ አላምንም… አሰልጣኝም ባትሆንም በሌላ ሙያ ላይም እንኳን መድረግ
የለበትም ይሄን ልንፀየፈው ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡-ይሄን ሰው ልገምት የአሁኑ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ መሆኑን
አረጋግጫለው
ዘማርያም፡- (ሳቅ) ለጊዜው ስሙን አልናገርም… ተወው ስሰጠው
እወስደወሃለው…(ሣቅ)
ሀትሪክ፡-በኛ ሀገር እግር ኳስ አሰልጣኝ መሆን ይመቻል?
ዘማርያም፡- ሙያውማ ደስ ይላል፡፡ ነገር ግን አሁን በአገሪቱ እንዳጠቃላይ ባለው
ወቅታዊ ሁኔታ ትንሽ ያስቸግራል አገሪቱ ሠላም ከሆነች… ሙያው መልካም ነው እኛ
ስንበስል ወደፊት የሚቀረፍ ይሆናል የኛ አቅም ጠንካራ አይመስለኝም፡፡ ሙያው በጣም
አጨናቂ ነው በጭንቀቱ ውስጥ ደስታ የምታገኝበት መሆኑ ያስደስታል እኔ በማመጣው
ውጤት ከጀርባ የሚደሰት ህዝብ አለ፡፡ በተለይ የከነማ ቡድኖች ብዙ ደጋፊ
አላቸው፡፡በታሪክ ገጠመኝ ከከነማ ክለቦች ውጪ አልሰራሁም የተለየ እድሉ እኔ በሰራሁት
ህዝብ ይደሰታል፡፡ ይሄ ዝም ብሎ አይገኝም፡፡
ሀትሪክ፡-የኛ ሀገር እግር ኳስ አድርጓል ማለት ይቻላል?
ዘማርያም፡-በፍፁም አደገ ልልህ አልችልም፡፡ እነ አሸናፊ ሲሳይ ሙሉጌታ ከበደ
ሲጫወቱ ጊዮርጊስ ደስ ይለኝ ነበር… ነገር ግን ሰፈራችን መሀንዲስ ስለሆነ የምድር ጦር
ደጋፊ ሆነን ነው የኖርነው፡፡ በዚያ ዘመን ያለውን እግር ኳስ ከአሁኑ ጋር ስታስተያየው
በየአመቱ አንድ ርምጃ ወደ ኋላ እየሄደ ነው፡፡ ምናልባት የዛሬ 20 እና 30 አመት ከሆነ
ኳሱ በዚያው ልክ ወደኋላ እየሄደ ነው ብዙ መሰራት ያለበት ነገር አለ፡፡
ሀትሪክ፡-ዳኝነቱን እንዴት አገኘኸው?
ዘማርያም፡-እግር ኳሱ ሲያድግ ዳኝነቱም በዚያው ደረጃ ያድጋል…. እርግጥ ኳሱና
ዳኝነቱን ካነፃፀርን ዳኝነቱ ይሻላል፡፡ በአለምና በአፍሪካ ደረጀ እነ በአምላክ ተሰማ እነ
ሊዲያ ታፈሰ የሚያደርጉትን ስታይ ዳኝነቱ ይሻላል የሀገራችን ዳኝነት ከእግር ኳሱ የተሻለ
ቢሆ|ንም የሚገባው ቦታ ደርሷል ማለት አይቻልም ኳሱ ቢያድግ ኖሮ ግን ዳኝነቱ ከዚህ
የተሻለ ያድግ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡-አሰልጣኞች ከተጨዋች ጋር ለማስፈረምም ሆነ ለማሰለፍ ገንዘብ ይወስዳሉ
ይባላል… ?
ዘማርያም፡-ይሄን ታሪክ በወሬ ደረጃ ሲባል ሰምቻለው አንዳንዶቹ የሚሄዱበት መንገድ
የተለየ በመሆኑሲ ሊያዙ አልተቻለም፡፡ እገሌ እንዲህ አደረገ ይባልና ማስረጃ የለም፡፡
አካሄዳቸው ምስጢራዊ በመሆኑ አልተያዙም፡፡ አካሄዱ ግን በጣም ያሳፍራል
አሰልጣኝነት ስጀምር ደመወዜ 1500 ብር ነበር፡፡ ከ10 አመት በኋላ ግን ከታክስ በኋላ
60 ሺህ ብር አገኛለሁ ወደ 90 ሺህ ብር በለው.. ይሄንን የሚያገኝ ሰው ተጨማሪ
ገንዘብ ያውም በግፍ ለማግኘት ለምን ይፈልጋል? በዚያ ላይ የፊርማ የጥቅማጥቅም
ክፍያ አለ… በዚህ ደረጃ ስታየው ደመወዙ ባላደገ እግር ኳስ እንደ መስረቅ ይቆጠራል…
ሀትሪክ፡-አንተንስ ለማባበል የሞከረ ተጨዋች የለም?
ዘማርያም፡-አልገጠመኝም፡፡ ተጨዋቾቹ ወደ አሠልጣኞቹ ከመሄዳቸው በፊት ለማን
ሊሰጡ እንደሚችሉ ማን በዚህ በኩል እንደሚመች አጥንተው ይመስለኛል ለዚህ ነው እኔ
ጋር ያልመጡት.. በርግጠኝነት ከመጣ ግን ትምህርት ሰጥቼው የምንለያይ ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡-በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ባይኖር ወይም ቢጠፋ የምትለው ምንድነው?
እያንጓለለ በእግር ኳሱ ላይ መግባቱን ታውቅ ነበር?
ዘማርያም፡- ፋሲል ከነማን ይዤ ዳሽን ቢራ አካባቢ ተመሳሳይ ነገሮችን ይነሱ ነበር…
ተጨዋቾቹ አመድ ተቀብተው ሜዳ ይወጡ ነበርና በጣም የሚያስደነግጥና እግር ኳስ
ሜዳ ላይ ያለህ አይመስልም ነበር… ፍፁም ያስደነግጣል በግሌ ግን ገጥሞኝ አያውቅም
ትኩረትም አልሰጠውም ነገሮቹ መኖራቸውግን ከባድ ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡-ማሊያ አጥበው እስኪደርቅ ይጠባበቃሉ ሰው እንዳይነካው ማለት ነው…
ጤነኛው ሜዳ ሲገባ እግሩ ያብጣል… ወዘተ አያስፈራም?
ዘማርያም፡- ይሄኮ በጣም ከባድ ነው ፈጣሪ እንጂ እኔ እንዴት ልመልሰው
እችላለው፡፡ ለኳሱ ትልቅ ህመም ይመስለኛል፡፡ በምንድነው የምታስታርቀው ተደረገብኝ…
ያለውና አደረገ የተባለው ብንይዛቸው ጠበል ይዘህ ነው የምታስማማው? ወይስ
ለማስታረቅ ከባድ ይመስለኛል በዚያ ላይ የቡድኑን ውጤታማነት ያበላሻል… አንድነታቸውን
ይሸረሽራል ይሄ ደግሞ ቤተሰባዊ ትብብራቸውና የማሸነፍ ሞራላቸውን ይገድላል ነገን
እንድትፈራ ያደርጋል…በዚያ ላይ ዘረኝነቱ ተጨምሮበት ሂደቱን የከፋ ያደርገዋል፡፡
አፍሪካዊያን ተጨዋቾች እንደልባቸው ሲጫወቱ የኛ ሀገር ተጨዋቾች ግን ከመጡበት
ዘር የተነሳ ይሳቀቃሉ፡፡ ከውጪ መጥቶ የዜግነት የብሔር ችግር የለበትም የውጪ ዜጋ
ነው የኛ ሀገር ግን ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ብሔር ነህ እየተባለ ተሸማቆ እነሱ ግን
የሚገባቸውን ደመወዝ አግኝተው ይኖራሉ ኦኪኪ አፎላቢ ከፍተኛ ብር ነው
የሚሰጠው.. ደረቱን ነፍቶ አካውንቴ ውስጥ ካልገባ አልጫወትም አለ.. ያለው
ገንዘብ ገብቶለት እንደልቡ ይጫወታል… የኛ ሀገር ተጨዋቾችኮ የዚህን አይነት መብት
የላቸውም ከመጣህበት አካባቢና ዘር መመዘን ያማል አይደለም ለኳሱ በወንድምነት
አብሮ ለመኖርም አደገኛ ችግር ይመስለኛል እንደ አጠቃላይ ሁለቱ ከላይ ያነሳኋቸው
ችግሮች ጠፍተው ማየት እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡-በኳሱ ህይወትህ የማትረሳው ገጠመኝ አለ?
ዘማርያም፡- አዎ….. አንድ ልጅ ነበር በብዛት ከ18ቱ ውጪ ይሆን ነበር አንድ ጊዜ
እንደነገ ባለ ግጥሚያ ላይ ላሰልፈው ወስኛለሁ… ልጁ ያው አልገባም ብሎ ወስኗል ሶስተኛ
ተመራጭ ግራ እግር ነው ሁለት የሚበልጡት ስላሉ አልገባም በሚል ማታ አምሽቶ
እየተዝናና ነው፡፡ በሳይክል ስሄድ የሆነ መዝናኛ ቦታ ላይ ከርቀት አየሁት.. ቁጭ ብሎ
እየተዝናና ነው… ነገር ግን ነገ ደግሞ ጨዋታ አለው… አሰብ አደረኩና ወደ ክለቡ ካምፕ
ገብቼ የህዝብ ስልክ አለ ደወልኩና አሰልጣኙ ስለገባ ቶሎ ና አልኩት ተጨዋች
መስዬዋለው… ትንሽ ቆይቶ እየሮጠ ሲገባ አይቼዋለው የፈለኩት ዕረፍት እንዲወስድ ብቻ
ነበርና ግቢው ውስጥ ጎርደድ ጎርድድ ስል አይቶኝ እውነት ነው ለካ አሰልጣኙ መጥቷል
ብሎ ወደ ክፍሉ ገብቶ ተኛ… ያሰብኩት ተስካቶልኝ በነጋታው ጨዋታ 4ለ1 ስናሸንፍ 2 ጎል
ያገባው እርሱ ነበር መቼም የማልረሳው ገጠመኝ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ካገርህ ውስጥም ይሁን ከውጪ የማን አድናቂ ነህ?
ዘማርያም፡- በልጅነቴ ስላገኘኝ ይሁን ለአሠልጣኝ ስዩም አባተ የተለየ ስሜት አለኝ፡፡
ወንጂ ላይ ለትንሽም ጊዜ ያሰለጠነኝ አብርሃም መብራቱንም አደንቃለው በተለይ
የአብርሃም ስብዕና ደስ ይለኛል፡፡ ከውጪ ብዙም የለም… ከአሰልጣኞች በላይ
የማን.ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ፡፡ አሰልጣኙ ማንም ቢሆን ግድየለኝም… በርግጥ ፔፕ ጋርዲዮላ
ደስ ይለኛል ግን የርሱ ቡድን ብዙ የኳስ ንክኪ ይበዛዋልና አይመቸኝም እኔ ደግሞ ቶሎ
ቶሎ ፕሬስ አድርጎ ወደ ጎል የሚሄድ ቡድን ደስ ይለኛል..እንዲያውም ከፔፕ ጋርዲዮላ
ይልቅ የሊቨርፑሉ የርገን ክሎፕ ይበልጥ ይመቸኛል፡፡
ሀትሪክ፡-ሜሲ ሮናልዶ…. የቱ ይበልጣል?
ዘማርያም፡- ሜሲ ለማለት ይቀለኛል… ተሰጥኦው ልዩ ነው በተፈጥሮ ያገኘው ነው
የሮናልዶ የስራ ውጤት ሳይዘነጋ…፡፡ ፈጣሪ ለሁላችንም ሰጥቶናል አያዳላም ግለሰቡ
የሚጨምረው ነገር ነው የሚለየው፡፡ የተፈጥሮ ችግሩን አልፎ ለስኬት በመብቃቱም
ለሜሲ ልዩ ፍቅር አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡-አሁን ስራ አቁመሃልና… ምን እየሰራህ ነው?
ዘማርያም፡-ገናኮ ነው 1 ወርም አልሆነኝም.. ጭንቀላቴም አላረፈም ረዳት
አሰልጣኞቼ እየደወሉ አማክራቸዋለው አዕምሮዬ አላረፈም… የጅማን ደረጃ ውጤት
እከታተላለሁ ከአሰልጣኞቹ ጋር አወራለው… ያን እያደረኩ ነው ባለቤቴንና ልጄን በደንብ
ነው ያገኘኋቸው… ልጄም የተወለደችው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ነውና ከነርሱ ጋር ዘና
እያልኩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ሌላ ክለብ ጥሪ ቢያደግልህ ለመነጋገር ዝግጁ ነህ?
ዘማርያም፡- የትም ቦታ ሄጄ ማሰልጠን እችላለው…. በውስጥ ውል ነው ያለሁት፡፡
ውሉ ፌዴሬሽን ገብቶ ቢሆን ኖሮማ የግድ ይከፍሉኝ ስለነበር አልቸገርም ነበር፡፡ አሁንም
ሰብዓዊነቱ ካለ ጅማ አባጅፋር ጋር ገንዘብ አለኝ…. ግልፅ የሆነ የ2 ወር ደመወዝ አለኝ
የፊርማ ግማሹን ብር ብወስድ እንኳ ከ1 ሚሊዮን ያላነሰ ገንዘብ አለኝ… ያንን ቢሰጡኝ
መልካም ነው በአጠቃላይ ፈላጊ ክለብ ከመጣ ሄዶ የመስራት ችግር የለብኝም ዝግጁ
ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-የመጨረሻ ቃል…?
ዘማርያም፡-በዋናነነት ለጅማ አባጅፋር ደጋፊዎች ነው… በግል ተነሳሽነት ክለቡን
ለቅቄ እንዳልወጣሁ ያውቃሉ ከአመራሮቹም ጋር ሠላም ነኝ ግንኙነታችን መልካም ነው
ቀሪውን የውድድር ዘመን የሚጨፍሩበት እንደሆን እመኛለው… እናንተን ጥዬ ለመውጣት
ከባድ ፈተና ገጥሞኝ እንደነበር መናገር እፈልጋለው፡፡ ለተጨዋቾቹም መናገር
የምፈልገው በሳል ልጆች ያሉበት ስብስብ ነው ከነመስኡድ ጋር የሰራሁት ግማሽ የውድድር
አመት ነው ሁልጊዜ ብሰራ የማልጠግበው ተጨዋች መስኡድ ነው፡፡ ከተጨዋች መማር
የምትችል ከሆነ ከመስኡድ ትማራለህ… እነ መስኡድም መልካም የውድድር ጊዜ
እንደሆንላቸው ቡድኑን አስተባብረው በጥሩ ደረጃ እንዲጨረሱ እመኛለሁ፡፡ ከጎኔ ያሉትን
ቤተሰቦቼን፣ ባለቤቴን፣ የሙያ አጋሮቼን የስፖርት ቤተሰቡን በኔ ጉዳይ ላይ ድጋፋቸውን
ላደረጉ በሙሉ ማመስገን እፈልጋለው….. ከሁሉ በላይ ግን ለልዑል እግዚአብሔር
ምስጋና አቀርባለሁ፡፡