ሶዶ የካቲት 8/2009 በአንደኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ውድድር በጨዋታ ሜዳዎች የታየው ስፖርታዊ ጨዋነት ከወትሮው መሻሻል ማሳየቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ፌዴሬሽኑ የ2009 ዓ.ም የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ 1ኛ ዙር ውድድር አፈጻጸም በወላይታ ሶዶ ገምግሟል።
- ማሰታውቂያ -
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ እንደገለጹት የ2009 ዓ.ም 1ኛ ዙር ፕሪሚየር ሊግ የወንዶች ውድድር በተለይ በስፖርታዊ ጨዋነት ከሌላው ጊዜ የተሻለ ሆኖ ተስተውሏል።
በሜዳ ደህንነት ዙሪያ የሚስተዋሉ የፀጥታና የደህንነት ስጋቶችን ለመፍታት ከክለቦች ጋር በጋራ መሰራቱ ለታየው መሻሻል አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
የፀጥታና የስፖርታዊ ጨዋነት ኮሚቴ በማቋቋም በተጫዋችም ሆነ በተመልካች የሚፈጠሩ የስነ ምግባር ጥሰቶች ዝርዝር በማውጣት በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ለአሰልጣኞች፣ ለቡድን መሪዎችና ለደጋፊ ማህበራት ኃላፊዎች ስልጠና መሰጠቱም ለመጣው ውጤት አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል ።
የስፖርት ቤተሰቡና የፀጥታ ኃይሎች ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ የተደራጀ አሰራር በመዘርጋት በኩል ክፍተቶች ቢኖሩም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት የተሻለ እንደሆነ አብራርተዋል።
“ይሁን እንጂ ችግሩ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ማለት አይቻልም፤ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል” ብለዋል።
በውድድር ዓመቱ በአንዳንድ ሜዳዎች የተመልካች ቁጥር አነስተኛ መሆን፣ የዳኝነት ስህተቶች፣ የመወዳደሪያ ሜዳዎች የተሟላና ምቹ አለመሆን በዓመቱ ካጋጠሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የፌዴሬሽኑ የውድድሮች ሥራ ሂደት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ናቸው ።
ከመርሀ ግብር አወጣጥ ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት ችግሮች ያጋጥሙ እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ “ከክለቦች ጋር በመወያየትና ተቀራርበን በመስራታችን መፍትሄ አምጥተናል፤ ወደፊትም እንቀጥላለን” ብለዋል።
የሁለተኛው የውድድር ዘመን በተያዘለት መርሀ ግብር ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ የተሟሏ ክትትል በማድረግ እግር ኳሱ እንዲያድግ እንደሚሰራ አመልክተዋል ።
ከጥቅምት 3 እስከ የካቲት 2 ቀን 2009 ዓ.ም በተካሄደው የ1ኛ ዙር የወንዶች ፕሪሜየር ሊግ ውድድር 16 ክለቦች መሳተፋቸው የሊጉ ኮሚቴ ሪፖርት አመላክቷል ።
በውድድሩ 434 ስፖርተኞች ፣ 29 አሰልጣኞች፣ 16 የቡድን መሪዎችና 16 ወጌሻዎች መሳተፋቸው ተጠቅሷል።
በፕሪሜየር ሊጉ 120 ጨዋታዎች በደርሶ መልስ እንደተካሄዱና 480 ዳኞች፣ 120 ኮሚሽነሮችና 600 አመራሮች ውድድሩን መምራታቸው ተገልጿል።
በውድድሩ 445 ቢጫና 23 ቀይ ካርዶች መታየታቸውም ተጠቁሟል።
በአንደኛው ዙር ፕሪሜየር ሊግ ውድድር ቅዱስ ጊዮርጊስ በ29 ነጥብ፣ ደደቢት በ27 ነጥብና እንግዳው ፋሲል ከተማ በ26 ነጥብ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ሲይዙ፤ ጅማ አባቡና፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና አዲስ አበባ ከተማ በወራጅ ቀጠና እንደሚገኙ ተገልጿል።
ከደደቢት ጌታነህ ከበደ በ11 ጎል፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አዳነ ግርማና ሳላሃዲን ሰይድ እንዲሁም ፍጹም ገብረማሪያም ከኤሌክትሪክ በተመሳሳይ በ7 ጎል ኮኮብ ግብ አግቢነቱን እንደሚመሩም ተመልክቷል፡፡