ለ29 ዓመታት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት ካሜሮናዊው ኢሳ ሀያቱ በቀጣይም የካፍ ፕሬዝዳንት ሆኖ የመመረጥ ዕድል እንዳላቸው ተናገሩ።
ኢሳ ሀያቱ ነገ በሚጀመረው 39ኛውየካፍ ጠቅላላ ጉባኤና በ60ኛው የካፍ የምስረታ በዓል ላይ ለመካፈል ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ገብተዋል።
የ70 ዓመቱ ኢሳ ሀያቱ በዚህ ወቅት ለጋዜጠኞች እንዳሉት ”የካፍ ፕሬዝዳንት ሆኜ በሰራሁባቸው ዓመታት ለአፍሪካ እግር ኳስ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ፤ በቀጣይ ምርጫም አሸንፋለሁ” ብለዋል።
ካፍ በዓለም የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽኖች በደንብ እንዲታወቅ፣ በዓለም ዋንጫና በአፍሪካ ዋንጫ የሚወዳደሩ ቡድኖች ቁጥር ከፍ እንዲል፣ የታዳጊዎችና የሴቶች ውድድር እንዲጀመር፣ እንዲሁም ካፍ የተሻለ በጀት እንዲኖረው መስራታቸውንም ነው ያስረዱት።
በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ክለቦች የሚሰጣቸው ሽልማት ከ500 ሺህ ዶላር ወደ አራት ሚሊዮን ዶላር ከፍ እንዲል ማድረጋቸውንም እንዲሁ።
በቀጣይ አራት ዓመታትም የካፍ ፕሬዝዳንት ለመሆን ኢሳ ሀያቱ ከማዳጋስካራዊው አህመድ አህመድ ጋር ይፎካከራሉ።
ፕሬዝዳንቱ ከካፍ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጋር በመሆን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር እርስቱ ይርዳ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጁነዲን ባሻና ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ኢሳ ሀያቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በቢሾፍቱ ያስገነባውን የእግር ኳስ አካዳሚ ዛሬ በእንግድነት ተገኝተው መርቀዋል።
አካዳሚው በቀድሞ የካፍ ፕሬዝዳንት ይድነቃቸው ተሰማ ስም መሰየሙ እንዳስደሰታቸው ሀያቱ ገልጸዋል።
“ይድነቃቸው የኔ አባት ነው፣ እሱን ተክቼ ነው ካፍን እየመራሁ ያለሁት ስለዚህ በአባቴ ስም የተሰየመውን አካዳሚ ለመመረቅ ወደ ቢሾፍቱ የማቀናው በደስታ ነው” ብለዋል።
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ እርስቱ ይርዳ በበኩላቸው “የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ መካሄዱ ለአገሪቱ እግር ኳስና ለቱሪዝም ዕድገት ትልቅ ፋይዳ አለው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ የካፍ መስራች እንደመሆኗ እና እንደ ፈርቀዳጅነቷ በአህጉር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተፎካካሪነት አመርቂ አይደለም።
ስለሆነም በቀጣይ በታዳጊዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ እርስቱ ተናግረዋል።
በጉባዔው የተለያዩ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ስለሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ክለቦች፣ የስፖርት አስተዳደሮችና ወጣቶች ልምድ የሚያገኙበት መድረክ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በ39ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ጠቅላላ ጉባኤ ከ500 በላይ እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።